አርበኞች ግንቦት 7 በሙስሊም እንቅስቃሴ መሪዎች ላይ የተሰጠውን ፍርደገምድል ውሳኔ እንደሚያወግዝ አስታወቀ

Ethiopian-Muslim-committee1

የህወሓት አገዛዝ የሚዘውረው የይስሙላ ፍርድ ቤት ዛሬ ሀምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በሙስሊም ወገኖቻችን መሪዎች ላይ ፍርደገምድል ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህ ውሳኔ መሠረትም የእምነት መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው በሰላማዊ በሆነ መንገድ የጠየቁ ወገኖቻችን መሪዎች እስከ 22 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል። ሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ሥርዓቱ ያደረገውን ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ተቋቁመው “ድምፃችን ይሰማ!” የሚል አቤቱታ ከማቅረብ የዘለለ አንዳችም የኃይል እርምጃ ወስደው አያውቁም። ሆኖም “በደል ደርሶብኛልና ልሰማ” ብሎ አቤቱታ ያቀረበ ሕዝብ መሪዎችን እስከ ሃያ ሁለት ዓመታት በእስር መቅጣት የአገዛዙ እብሪትና ማናለብኝነት አጉልቶ የሚያሳይ ተግባር ነው። አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህን ፍርደገምድል ውሳኔ አጥብቆ ያወግዛል።ይህ ፍርደገምድል ውሳኔ የተሰጠው ፕሬዚዳንት ኦባማ በአገራችን መዲና ተገኝተው “ለሰላም ሲባል ነፃነትን ማፈን ሁለቱንም ያሳጣል” ባሉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ አገዛዙ የሚሰማ ጆሮ የሌለው መሆኑ የሚያረጋግጥ ሆኗል። የሙስሊም መሪዎች በእስር ላይ በነበሩት ጊዜ በምርመራ ስም ተደብድበዋል፤ ክብራቸው ተደፍሯል፤ የተለያዩ ዘግናኝ ሰቆቃዎች ተፈጽሞባቸዋል፤ የሀሰት ዶክመንታሪ ፊልሞች እንዲሰራጩ ተደርገው ስማቸውን ለማጥፋት ሙከራ ተደርጓል። በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የደረሰው በደል ሃይማኖት ሳይለይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰ በደል ነው፤ መፍትሄ የምናገኘውም በጋራ በምናደርገው ትግል ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና የአገር አንድነት የሚጠብቅ የመንግሥት ሥርዓት ስናቆም ነው። ከዚህ በመለስ የሚገኝ መፍትሄ የለም። የእምነት መብቶች የሚከበሩት ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ሲከበሩ እንደሆኑ “በድምፃችን ይሰማ” ሥር የተሰባሰቡ ወገኖቻችን ይረዳሉ ብለን እናምናለን።

አርበኞች ግንቦት 7 ሙስሊም ወገኖቻችን ለዓመታት ያለመታከት ያካሄዱትን ትግል ያደንቃል። ከእንግዲህ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ ተደጋግፈን በመታገል ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ለሁላችንም የምትመች አገር እንድንገነባ ጥሪ ያደርጋል። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ ጋር ዕሁድ እለት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ ምን ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል በሚል አስቀድሞ ከሕብር ሬዲዮ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ በንጹሃን የኮሚቴ አባላቱ ላይ ሕወሃት የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ የሚወስነው ስርኣቱ ያለበትን ጫና መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጿል። <…ምን አልባት ከሶስት እስከ አምስት ኣመት ሊፈረድ ሆን ተብሎ ሊፈረድ ወይም የተለመደው አይነት የጭካኔ ፍርድ ለመፍረድ መሞከር ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ተነጣጥሎ በማይኖርባት አገር በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ላይ መፍረድ ነው ይህም ውሳኔ አለመረጋጋት ሊያመጣ ይችላል..>> ሲል ገልጻል።

ከጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ ጋር ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ ጨምሮ ወቅታዊ ልዩ ልዩ ህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችንና በዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 


 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *