- ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ለስልጣን ለሚያሰጋው ድርጅትና ተቋም ለራሱ ስልጣን የሚበጀውን ሌላ ድርጅትና ተቋም በመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ ልዩነት ከፋፍሎ ሲገዛ ቆይቷል፡፡ ለመምህራን ማህበር ለመምህራን ሳይሆን ለእሱ የሚመች ማህበር፣ ለፖለቲካ ድርጅቶች ለህዝብ የሚቆም ሳይሆን ለአገዛዙ መሳሪያ የሚሆን ድርጅት፣ ለሰብአዊ መብት ድርጅቶችም እንዲሁ ለኢትዮጵያውያን የሚቆሙ ሳይሆን ከእሱ ጋር የሚወግኑ ድርጅቶችን በማቋቋም እውነትና ከእውነተኞችን ሲታገል ኖሯል፡፡ ከዚህም አልፎ አሁን በሀይማኖት ውስጥ ለእሱ የሚመች ሌላ ሀይማኖት በመቋቋም ላይ ነው፡፡
የቆየው የአገዛዙ እኩይ ባህሪ ስልጣን ላይ ለመቆየት በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ በሀይማኖት ተቋማትም ጭምር ጣልቃ በመግባት እሱ የሚፈልገውን እምነት በመደገፍ፣ ሌላው ላይ ቅጣት በመጣል ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም አገዛዙ ባለፉት ሶስት አመታት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ እያደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት መመልከት በቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ኢህአዴግ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብ ንቅናቄ ማድረግ በጀመሩበት ወቅት ስርዓቱ ለመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው እውቅና ሰጥቶ ሲደራደር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁንና በሚፈልገው መንገድ አልሄድለት ሲል የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴ አባላትን አስሯል፡፡ ‹‹አሸባሪ›› ብሎ ከሷል፡፡ ሀምሌ 27/2007 ዓ.ም እውቅና ሰጥቶ ሲደራደራቸው የነበሩትን የሙስሊሙ ማህበረሰብ አመራሮች ከ7 እስከ 22 አመት እስራት ፈርዶባቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ‹‹ሽብር›› የሚባለው ክስ ስርዓቱ ያልፈለገውን የሚያስርበት መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ክስ ሰላማዊ ታጋዮችን ጥፋተኛ የሚለው ፍርድ ቤትና ህግም የአገዛዙ ዋነኛ መሳሪያ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ የፖለቲካ ሰነድ ከሆነው ህገ መንግስት ላይ በቅዳሚነት ከሚሰፍሩት መብቶች መካከል አንዱ የሆነው የሀይማኖት (የሰብአዊ መብት) ጥያቄ እንደሆነ ያምናል፡፡ ይህም በመሆኑ ስርዓቱ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህን እመን፣ ይህን አትመን በሚል እምነት ወደመወሰን ጣልቃ ገብነት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ትክክል እንዳልሆነ ለማስገንዘብ ጥሯል፡፡ ሆኖም ለሀገርና ለህዝብ ከሚጠቅመው ሀሳብ ይልቅ የስልጣኑ ጉዳይ ብቻ የሚያሳስበው ኢህአዴግ የሚሰማ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ኢህአዴግ ሰላማዊ ታጋዮችን በፈጠራ ሽብር ወንጀል ከሶ ሲያስር፣ ለፖለቲካ ድርጅቶችና ለተቋማት ለእሱ የሚመቹትን በመፍጠር አባዜው ሀገራችንን አደጋ ውስጥ እየጣላት ይገኛል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሌላ አደጋ ውስጥ እንድንገባ እያደረገም ነው፡፡
ከአሁን ቀደም ካሉት በርካታ ተሞክሮዎች ለመረዳት እንደሚቻለው አገዛዙ ምክርና ትችት አዳምጦ ማስተካከያ ከማድረግ ይልቅ በእልህና በማን አለብኝነት እያባባሰ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ አሁንም በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የፈፀመው በደል ተተችቶ የሚያስተካክለው ነው ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ ይልቁንም ሀገራችንን አደጋ ላይ ለመጣል በየ ጊዜው የፈፀማቸውና ወደፊትም ለመፈፀም ወደኋላ የማይላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ብቸኛው አማራጭ በጋራ መታገል ነው፡፡ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ስርዓቱ እንደመሆኑ ለየብቻችን የምናስመልሳቸው መብቶች አይኖሩም፡፡ የሰብአዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ልናስከብር የምንችለው ዋነኛው የችግሮቹ ምንጭ የሆነውን ስርዓት ታግለን ለኢትዮጵያችን የሚበጅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስንገነባ መሆኑን ተገንዝበን ሰላማዊ የነፃነት ትግሉን መቀላቀል ይኖርብናል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አገዛዙ እየፈፀመበት ያለውን በደል በመቃወም ሲያደርግ የቆየውን ሰላማዊ ትግል ያደንቃል፡፡ በኮሚቴው ላይ የተወሰደው እርምጃ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ይበልጡን ትግሉን አጠናክሮ፣ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ተባብሮ አምባገነንነትን ከምንጩ ከማድረቅ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ በመሆኑን ሰላማዊ ትግሉን በመቀላቀል በሰብአዊነታችን፣ በዜግነታችን ከዚህም አለፍ ሲል በሀገራችን ላይ እየፀመው ያለውን አደጋ በመገናዘብ፣ የፖለቲካ ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኑ! ራሳችን ነፃ በማውጣት የሀገራችንን እጣ ፋንታ እንወስን!
ሀምሌ 29/2007 ዓ.ም አዲስ አበባ
ህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።