የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ነገ ለብይን ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ፣ዕድር ላይ ጥያቄ የጠየቁ የሰማያዊ የፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ ታሰሩ

የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ወደ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ  በወታደሮች አጀብ
የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ወደ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በወታደሮች አጀብ

 

(ህብር ሬዲዮ-ላስ ቬጋስ) የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ላለፉት አስራምስት ወራት በእስር ቤት በቆዩበት የፈጠራ ወንጀል ላይ ልደታ የፌዴራሉ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ብይን ለመስጠት ነገ ነሐሴ 14 ቀን 2007 አስቀድሞ በሰጠው ውሳኔ መሰረት ይቀርባሉ። በነገው ችሎት ብይኑ ይሰጣል ወይም ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ተለዋጭ ቀጠሮ ይስጡ ከወዲሁ የታወቀ ነገር የለም።

በነገው በእስር ላይ በቀሩት የዞን ዘጠኝ ጦማሪአንና ከአገር ውጭ ባለችው ሶሊያና ሽመልስ ላይ የቀጠለው የክስ ሒደት ለብይን የተቀጠረው ተከሳሾች በተጠረጠሩበት ወንጀል በነጻ ይሰናበቱ ወይም ጥፋተኛ ናቸው ይከላከሉ ለማለት ሲሆን የፕ/ት ኦባማን የኢትዮጵያ ጉዞ ተከትሎ በተመሳሳይ ክስ በአንድ መዝገብ ተከሰው ከነበሩት አምስት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።

ለነገው የብይን ቀጠሮ በእስር ላይ የሚገኙት ናትናኤል ፈለቀ፣በፍቃዱ ሃይሉ፣ አቤል ዋበላና አፍናፍ ብርሃኔ ሲሆኑ የክስ መዝገቡ በስሟ የሚጠራው ሶሊያና ሽመልስ በሌለችበት እንደተለመደው ጉዳዩዋ ይታያል።

አስቀድሞ በተመሳሳይ የፈተራ ክስ ታስረው ከነበሩት ጦማሪያን መካከል ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ፣ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ፣ ጦማሪ ዘላለም ክብረት፣ማህሌት ፋንታሁንና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ ነሐሴ 2 ቀን 2007 በፍትሕ ሚኒስቴር ውሳኔ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መፈታታቸው ይታወሳል። ከእስር ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ ምልልስ ተመልሼ እታሰራለሁ የሚል ስጋት እንዳለው መግለጹ አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እድር ላይ ጥያቄ አንስተዋል የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ መታሰራቸውን ገነረ ኢትዮጵአ ዘገበ።በባሌ ዞን ሰልጣ ቀበሌ፣ ሲናና ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ የፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ ወርቅነህ ጋድይ አያና የእድር ስብሰባ ላይ ጥያቄ ጠይቀሃል ተብለው መታሰራቸውን የሰማያዊ ፓርቲ የዞኑ አስተባባ አቶ ደመላሽ በቀለ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ በተለይ ከምርጫው በኋላ ካድሬዎች አቶ ወርቅነህ እድርን ጨምሮ ከማህበራዊ ጉዳዮች እንዳይሳተፉ ጫና ሲያደርጉባቸው እንደነበረም ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም የአካባቢው ህዝብ ‹‹በፖለቲካ መሳተፍ ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው፡፡ እድር ደግሞ ማህበራዊ መብቱ በመሆኑ መሳተፍ አለበት›› በማለቱ እስካሁንም የእድር አባል ሆነው ቢቀጥሉም በእድሩ አካሄድ ጥያቄ አለኝ በማለታቸው ‹‹ለምን ጥያቄ ትጠይቃለህ?›› ተብለው እንደታሰሩ አስባባሪው ገልፀዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ ጋድይ በአሁኑ ወቅት በሲናና ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የአስተዳደር አካላት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ በሚፈፅሙት በደል ምክንያት ከትግል ውጭ ፍትህ እናገኛለን ብለው እንደማያምኑ አቶ ደመላሽ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *