አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት ለተደረገውና ለዋናው (ለሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ነሃሴ 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ለነሃሴ 22/2007 ዓ.ም ለውሳኔ ተቀጠሯል፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማቅረቡ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ሲል ነገረ ኢትዮጵአ ዘግባል።
አቶ ማሙሸት በአዲሱ ክስ የአቃቤ ህግን ምስክሮች ለመስማት ከ5 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት እንደተመላለሰ የተገለፀ ሲሆን በተለይ አንዱ ምስክር በፖሊስ ተይዞ እንዲመጣ ቢጠየቅም ፖሊስ ሳያስፈፅም ቀርቷል፡፡ ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሶስቱ ዛሬ የመሰከሩ ሲሆን ‹‹አቶ ማሙሸት አማረ 300 ብር ከፍሎ ሰልፍ እንድንወጣ አድርጎናል›› ሲሉ መስክረዋል፡፡ ይሁንና ምስክሮቹ ከማሙሸት ጋር በተገናኙበት ወቅት እንዲሁም ገንዘቡ ሲሰጣቸው፣ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ሲጠየቁ ‹‹አላስታውሰውም›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር የምስክርነት ቃል ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡
ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ አቶ ማሙሸትን ያስያዙ ደህንነቶች መሆናቸውን አቶ ማሙሸትና ጠበቃው በችሎቱ የገለፁ ሲሆን ምስክሮቹ በበኩላቸው ስራቸውን ሲጠየቁ ‹‹የግል›› እያሉ ከመመለስ ውጭ የመንግስት ስራ እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ሲጠየቁ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ ከሶስቱ ምስክሮች መካከል አንደኛው ስራውን ሲጠየቅ ‹‹የግል›› ብሎ የነበር ቢሆንም በመስቀለኛ ጥያቄ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጥቃቅንና አነስተኛ አመራር መሆኑን አምኗል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ የመኢአድ ደጋፊዎች መሆናቸውን ሲጠቅሱ አንደኛው አቶ ማሙሸት ባቀረቡበት የመስቀለኛ ጥያቄ ከምርጫ በኋላ የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል መሆኑን አምኗል፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኖም ቢሆን መኢአድን እንደሚደግፍም ገልጾአል፡፡
ዳኛው ‹‹በሁለት ወር ውስጥ እንዴት ብለህ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን ቻልክ?›› ሲሉት መልስ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡ የአቶ ማሙሸት አማረ ጠበቃ ሶስቱም ምስክሮች አብዛኛዎቹን ጉዳዮች እንደማያስታውሱ በመግለፃቸው የተጠና የምስክርነት ቃል መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ7 አመት በላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረው መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰልፉ አመራባቸው የተባሉትን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው፣ መተዳደሪያ ስራቸውን መደበቃቸውና መታወቂያ ለማሳየትም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምስክርነቱ የሀሰት እንደሆነ ስለሚያረጋግጥ ደንበኛቸው በነፃ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ቀጠሮ ህብር ሬዲዮ ሁኔታውን አስመልክቶ አቶ ማሙሸት አማረና ሌሎች አይ.ሲ.ስን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ዛሬም ከእስር ቤት ፍርድ ቤት እየተጉላሉ ነው ብለን መዘገባችን ይታወሳል። በጊዜው የጠቀስነው ዘገባ አያይዘን አቅርበነዋል።
አይ ኤስ አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰሩት እነ ማቲያስ መኩሪያ ለነሃሴ 18/2007 ዓ.ም እንደተቀጠረባቸው ነገረ ኢትዮጵአ ዘገበ፡፡ ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ ወቅት ‹‹የቪዲዮ ማስረጃም አለን›› በማለቱ ተከሳሾቹ ‹‹ቪዲዮው ይቅረብልን፡፡ የቪዲዮ ማስረጃው ለእኛም የመከላከያ ምስክርነት ይጠቅመናል›› ብለው ጠይቀው የነበር በመሆኑ፤ ፍርድ ቤቱ የቪዲዮ ማስረጃው መቅረብ እንዳለበትና እንደሌለበት ብይን ለመስጠጥ ለዛሬ ነሃሴ 5/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና የመናገሻ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት የማይሰራ በመሆኑ ችሎቱ በአራዳ ፍርድ ቤት በተረኛ ዳኛ ታይቷል፡፡ የልደታ ፍርድ ቤትም ‹‹ጉዳዩ አልተመረመረም፡፡›› በሚል ብይን ለመስጠት ለነሃሴ 18/2007 ዓ. ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቪዲዮው ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሲሰጥ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ተከሳሾቹም እየተጉላሉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ማቲያስ መኩሪያ ‹‹በቪዲዮው ጉዳይ ለመወሰን ለሶስተኛ ጊዜ ሲቀጠር ነው፡፡ እኛም ቤተሰቦቻችንም እየተጉላላን ነው፡፡›› ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ በተመሳሳይ 2ኛ ተከሳሽ መሳይ ደጉሰው ‹‹ድሃ ቤተሰብ አለን፡፡ ቤተሰቦቻችን መርዳት እንዳንችል እየተጉላላን ነው፡፡›› ብሏል፡፡ በማቲያስ መኩሪያ መዝገብ የተከሰሱት 1ኛ ማቲያስ መኩሪያ፣ 2ኛ መሳይ ደጉሰው፣ 3ኛ ብሌን መስፍን፣ 4ኛ ተዋቸው ዳምጤ ሲሆኑ ከመሳይ ደጉሰው ውጭ ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በአራዳ ፍርድ ቤት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው አቶ ማሙሸት አማረም ለነሃሴ 20/2007 ዓ.ም ተቀጥሮበታል፡፡ አቶ ማሙሸት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ‹‹ምስክሮቹ ስላልተሟሉና ብዙ መዝገቦችም ስላሉ ምስክርነት መስማት አልቻልንም›› በሚል ምስክሮቹ ሳይሰሙ ቀርተዋል፡፡ በተጨማሪም የአንድነት አባልና የሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ አምደኛ የነበረው እስማኤል ዳውድ አራዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለነሃሴ 28/2007 ዓ.ም ተቀጥሮበታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹‹በክረምት ከማይሰሩ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች መዝገቦች በመምጣታቸው ምስክር መስማት አልቻልንም፡፡ ስራ በዝቶብናል›› በሚል በበርካታ ተከሳሾች ላይ ረዘም ያለ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን በተለይ በሰልፉ ሰበብ የታሰሩ ተከሳሾች በተለይም ሴቶች እና ቤተሰቦቻቸው የተፋጠነ ፍርድ ልናገኝ አልቻልንም በሚል ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ሲያለቅሱ ተስተውለዋል ሲል ይሄው ነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ያስረዳል።ይህ በእንዲህ እንዳለ በስልታን ላይ ያለው አገዛዝ አይ.ሲስን ለመቃው አደባባይ ከወቱት መካከል ተቃዋሚ አላቸውን አፍሶ.አንዳንዶቹም በሰልፉ ባይገኙም ተቃዋሚ በመሆናቸው ብቻ በሀሰት ክስ ተለጥፎባቸው በእስር እየማቀቁ ሲሆን አይ.ሲ.ስን ለመቃወም ወጥተው ሶስት ኣመት በሌላ ፍርድ ቤት የተፈረደባቸው እንዳሉ ከዚህ ቀደም መዘገባችን አይዘነጋም።
አቶ ማሙሸት አማረ የመኢአድ ሕጋዊው ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ግንቦት 5 ቀን 2007 ከቤታቸው ሲወጡ በአገዛዙ ደህነቶች ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን በጊዜው በእስር ላይ እንዳሉ የቀረበባቸው ክስ አይ.ሲ.ስን ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ ተቃውሞ አስነስተሃል ሚል ሲሆን ለዚህም ክስ ሶስት የአገዛዙ ሀሰተኛ ምስክሮች ተሰምተዋል። አቶ ማሙሸት መከላከያ ባቀረቡበት ወቅት በዕለቱ ሰልፉ ላይ ሳይሆን ሕገ ወጥ ውሳኔ ወስኖ ከመኢአድ ጽ/ቤት በፖሊስ ያባረራቸውን ምርጫ ቦርድ ከሰው ፍርድ ቤት እንደነበሩ በማስረጃ ከልደታ ፍርድ ቤት አጽፈው ሲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ክሱ ተቋርጦ ይፈቱ ብሎ ማዘዙን ዘግበን ነበር።በጊዜው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይከበር ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት የተወሰዱት አቶ ማሙሸት ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ የፈጠራ ክስ ቀርቦባቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ። ሁለተናው ፍርድ ቤት አቶ ማሙሸት በአይ.ሲስ. ልጆቻቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ለቅሶ ደርሰው ወታቶችን ለአመጽ አደራጅተዋል የሚለው ላይ ተደጋጋኒ የጊዜ ቀጠሮ የቀረበውን ባለመቀበል በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ቢወስንም አገዛዙ ፍርድ ቤትን ሲፈልገው ማጥቂያ በመሆኑ ውሳኔውን ሳያከብር ላለፉት ሶስት ወራት ከእስር ቤት እስር ቤትና የይስሙላው ፍርድ ቤት እንደሌሎቹ የህሊና እስረኞች እየተጉላሉ ይገኛሉ።
ህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።