አቶ ማሙሸት አማረ ፍርድ ቤት በነጻ ከለቀቃቸው ያለ አንዳች ምክንያት ለአምስት ተጨማሪ ቀናት ታስረው ትላንት ቢፈቱም ዛሬም ባሉበት ቤት አካባቢ በፍርድ ቤት በሀሰት የቆሙባቸውን ጨምሮ ሌሎች የደህነት አባላት ክትትል እያደረጉ እንዳሉ ከመውጣታቸውም በፊት በእስር ላይ ሳሉ <<አንተን ከዚህ በሁዋላ አስረን የሚዲአ መነጋገሪያ አናደርግም አርፈህ የማትቀመጥ ከሆነ በማንኛውም ሰዓት እናስወግድሃለን>> እንዳላቸው ገልጸዋል። እስኪገሏቸው ድረስ የጀመሩትን ሰላማዊ ትግል አጠናክረው እንደሚገፉበት ለህብር ሬዲዮሶስት ወር ከሃያ ሁለት ቀን እስር በሁዋላ ከእስር ቤት እንደወጡ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገለጹ።
ከምርጫ 97 በፊትና በሁዋላ ከቅንጅት መሪዎች አንዱ ሆነው የታሰሩትን ጨምሮ ለስምንት ጊዜያት በተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው የተንገላቱት አቶ ማሙሸት አማረ ሕጋዊው የመኢአድ ፕ/ት ሲሆኑ ምርጫ ቦርድ በሕገወጥ መንገድ ፓርቲውን ለተለጣፊው የእነ አቶ አበባው መሐሪ ቡድን ሲያስረክብ ከቢሮ ተባረው ቦርዱን ከሰው በክርክር ላይ ሳሉ ግንቦት 5 ቀን 2007 ከቤታቸው አቅራቢያ በደህነቶች ታፍነው መታሰራቸው ይታወሳል።በተደጋጋሚ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ሲቀርቡ ከእስር ቤት እስር ቤት ሲመላለሱና ሁለቴ በነጻ አንዴ በዋስ ይፈቱ ተብለው ሳይፈቱ መቆየታቸውን በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው አብራርተዋል።
<<በእስር ቤት ከዚህ ወጥተህ እንቅስቃሴ ብታደርግ እናስወግድሃለን ከዚህ በሁዋላ አንተን አናስርም>> የሚል ጠበቅ ያለ ማስፈራሪያ የተሰጣቸው አቶ ማሙሸት አማረ <<በማንኛውም ሰዓት ሊገድሉኝ ይችላሉ ትግሉን ግን እስከመጨረሻው አላቆምም።በጀመርኩት ሰላማዊ ትግል እቀጥላለሁ >> ብለዋል።
አገዛዙ ከግንቦት 16ቱ ምርጫ በፊት እሳቸውን ባሰረበት ወቅት በምርጫው ላይ ችግር ስለሚፈጥሩ እንዳይፈቱ ሲል ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁን ያወሱት አቶ ማሙሸት እሳቸውም ሆነ ዛሬም ድረስ በአዲስ አበባና በክልል እየታደኑ የታሰሩ የመኢአድ አመራሮችና ጠንካራ አደራጆች ለአገዛዙ ስጋት ስለፈጠሩና መኢአድን ለማፍረስ የተደረገ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።
<<በሃያ አራት ዓመት ውስጥ አንድ ዳኛ የተቀነባበረውን የፈጠራ ክስና የተዘጋጁትን የሀሰት ምስክሮች በማየት ምስክርነቱን ውድቅ አድርጎ በነጻ ይፈታ ሲል አምስት ቀን ሳልፈታ ቆይቻለሁ>> ያሉት አቶ ማሙሸት ለኢትዮጵአ ሕዝብ እኩልነት ለሕግ የበላይነት የሚያደርጉትን ትግል በእንገድልሃለን በሚለው ዛቻ እንደማይተውና ሰላማዊ ትግሉን የሚከፈለውን መስዋዕትነት እየከፈሉ እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል። በማንኛውም ጊዜ ሊገድላቸውም ሆነ መልሰው በፈጠራ ሊያስሯቸው እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።ዛሬም በተለያዩ እስር ቤቶች ያሉ የሕጋዊው መኢአድ አመራሮችና ጠንካራ አባላት እንዲፈቱ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸው እሳቸውን ጨምሮ የታሰሩት ሁሉ በአገዛዙ በኩል ሲጠየቁ የነበረው ምርጫ ቦርድ <<መኢአድ>>የሚለውን ስምና ቢሮ ያስረከባቸውን አቶ አበባው መሀሪ ጋር ለምን አብራችሁ አትሰሩም የሚል ጭምር እንደነበር ገልጸዋል።
በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አለው ሕዝብ ትግሉ ሞቀ ቀዘቀዘ ሳይል ጠንክሮ የሚፈለገው የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲአዊ ለውት እስኪመጣ መደገፍ መስዋዕት የሚከፍሉትን በርቱ ማለት አለበት ብለዋል። ከአቶ ማሙሸት አማረ ሕጋዊው የመኢአድ ፕ/ት ጋር ከእስር እንደወጡ ያደረግነውን ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ ሰሞኑን ይዘን እንቀርባለን።
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።